የአማራ ክልል ፍትህ ቢሮ የ2016 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጻም አደረገ፡፡

የአማራ ክልል ፍትህ ቢሮ የ2016 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጻም አደረገ፡፡

ከነሐሴ 02-3/2016፣ ባህር ዳር፣ በአፈጻጸም ግምገማው የቢሮ ኃላፊዎች፣የማኔጅመንት አባላት፣ዐቃብያነ ህግ እና የአስተዳደር ሠራተኞች እንዲሁም የአማራ ክልል የፍትህ ባለሙያዎች ማሰልጠኛና የህግ ምርምር ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ተገኝተዋል፡፡

የቢሮ ኃላፊው አቶ ብርሀኑ ጎሽም የግምገማ መድረኩን ሲከፍቱ፤ ክልሉ በሁከትና በብጥብት የነበረ መሆኑን አውስተው በዚህ አስቸጋሪ እና ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ሆነን ስራችንን ለማከናወን ጥረት አድርገናል፤ውጤትም ማስመዝገብ ችለናል ብለዋል፡፡የተገኘው ውጤትም ሁላችንም ባደረግነው ርብርብ፣ ጥረት እንዲሁም ቁርጠኛ ሆነን መስራት በመቻላችን ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የዚህ መድረክ አላማ በዓመቱ ልንተገብራቸው በዕቅድ ይዘናቸው የነበሩ እና የተከናወኑ ተግባራትን በዝርዝርና በጥልቀት ገምግመን ጥንካሬዎችን እና ድክመቶችን የምንለይበት ነው ብለዋል፡፡ አክለውም ኃላፊው የለየናቸውን ድክመቶች በማረም፤ጥንካሬዎችን ደግሞ የበለጠ በማጠናከር ለ2017 በጀት ዓመት የዕቅድ አካል አድረገን ልንሰራ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡

የዕቅድ አፈጻጸሙ በበጀት ዓመቱ መጀመሪያ ላይ በዕቅድ ተይዞ ከነበረው እና ከቀደሙት ዓመታት ጋር በንጽጽር ቀርቧል፡፡አፈጻጸሙም ዝቅ ያለ ውጤት ያለው ቢሆንም ክልሉ ከነበረበት የሰላም እጦትና ከነበረው ፈታኝ ሁኔታ የፍትህ ተቋማትም በአስቸጋሪ ውስጥ ከማለፋቸው አኳያ ሲታይ የተሰራው ስራና የተገኘው ውጤት በሁሉም ዘርፍ ጥሩ ሊባል የሚችል እንደሆነ ከቀረበው የዕቅድ አፈጻጸም መረዳት ተችሏል፡፡

በአጠቃላይ በአፈጻጸሙ ላይ የታዩ ጥንካሬዎች እና ድክመቶች በዝርዝር ተለይተው ቀርበዋል፡፡አንኳር ተብለው ከተለዩት ጥንካሬዎች መካከል ቀደም ሲል ተጀምረው የነበሩ ስራዎችን ለማጠናቀቅ ትኩረት ሰጥቶ በመሰራቱ ለውጤት ማብቃት መቻሉ፣ ለፍትህ ስርዓቱና ለተቋሙ ሊያግዙና ሊጠቅሙ የሚችሉ አዳዲስ አሰራሮች መጀመር መቻሉ፣ ቀደም ሲሉ ተጀምረው የነበሩ እና ለፍጻሜ ያልበቁ እንዲሁም በአዲስ የተጀመሩት በሚከናወኑበት ጊዜ የተገኙ መልካም ተሞክሮዎች ማስቀጠል መቻሉ የሚሉት ከተዘረዘሩት በጥቂቱ ይገኙበታል፡፡

በአንጻሩ ደግሞ የፍትህ ሪፎርም ስራውን በእውቀት፣ክህሎት በአመለካከት እንዲሁም በቁርጠኝነት ይዞ ያለመስራት፣ ትላልቅ ጉዳዮችን ለይቶ በትኩረት ያለመስራት፣ከተለመደው አሰራር ለመውጣት መቸገርና አዳዲስ አሰራሮችን ፈጥኖ ያለመላመድ፣ በህገ-ወጥ መንገድ የተዘረፈ ሀብትን ትኩረት በሚፈለገው ልክ ያለማስመለስ፣ ልዩ ድጋፍ ለሚሹ የህብረተሰብ ክሎች የሚሰጣቸውን አገልግሎት በፍትሐብሔር ረገድ ውጤቱን ፈትሾ ያለማወቅ፣ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጅ አጠቃቀም ላይ ክፍተት መኖሩ፣ የባለሙያውን እውቀት፣ ክህሎት እና ሥነ-ምግባር የለየ ተከታታይ የህግ ኦዲት ስራ ያለመስራት ፣ በየደረጃው ያለው አመራር የሚመራውን የሰው ኃይል በጥልቀት አውቆ የመምራት ውስንነት የሚሉት እንደ ዋና ድክመት ተብለው ተለይተው ቀርበዋል፡፡

በቀረበው ዝርዝር የዕቅድ አፈጻጸም እና በጥንካሬ በተለይም ድክመት ናቸው ተብለው በተነሱት ላይ ሰፋ ያለ ውይይት ተደርጓል፡፡

ተሳታፊዎችም የሚቀርቡ አቤቱታዎች በአግባቡ ታይተው የመጨረሻ እልባት ወይም ምላሽ ስለማግኘታቸው ማረጋገጥ፣ ያላግባብ የሚመዘበረው የመንግስት ሀብት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት በመስራት መከላከል፣በህግ ተጠያቂ ማድረግ እንዲሁም ሀብቱን የማስመለስ ስራ በቁርጠኝነት ይዞ መስራት፣ሥነ-ምግባር በጎደላቸው ባለሙያዎች ምክንያት የሁሉም ባለሙያ እና የተቋሙ ስም ሊጎድፍ ስለማይገባው በነዚህ ላይ የእርምት እርምጃ መውሰድ፣ጠበቆች ለፍትህ ስርዓቱ መጎልበት ያላቸው ሚና ከፍ ያለ ነው፡፡ ስለሆነም ድጋፍና ክትትል ማድረግ ይገባል፡፡ ሙያው ከሚፈቅደው ውጭ በሚሰሩት ላይም እርምጃ መውሰድ፣የምስክር አበል አከፋፈል ላይ ከፍተኛ ችግር እየገጠመ በመሆኑ ትኩረት ሰጥቶ ችግሩን መፍታት፣የፖሊስ አባላት መደበኛ ስራቸውን እየሰሩ ባለመሆኑ በኛ ስራ ላይም ችግር እየገጠመን ስለሆነ ከሚያስከትለው ችግር አኳያ ተነጋግሮ መደበኛ ስራቸው ላይ ትኩረት ሰጥተው የሚሰሩበት ሁኔታ መፈጠር፣በሌላ በኩልም ፖሊስ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በትኩረት ተይዞ ከሚመለከታቸው ጋርም በመሆን ድርጊቱን ማስቆም፣ በተቋሙ የሚሰሩ ስራዎች ለህብረተሰቡ ተደራሽ እንዲሆኑ ማድረግ፣ የለውጥ ስራዎችን ትኩረት ተሰጥቷ መስራት፣ በሚታየው የስርዓት አልበኝነት ህብረተሰቡ በፍትህ ስርዓቱ ላይ አመኔታ እንዳይኖረው የሚያደርግ በመሆኑ በቁርጠኝነት መስራት፣ የሚሉት በርከት ያሉ አስተያየቶች ተሰጥተዋል፡፡

በመጨረሻም በቀረበው የዕቅድ አፈጻጸም እና በተሰጡ አስተያየቶች ላይ ዘርፉን በሚመሩት እና በቢሮ ኃላፊው የተሰጡ አስተያየቶች ጠቃሚ በመሆናቸው መወሰድ እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top