”የፍትሕ አገልግሎት በቅብብልሽ እና በትብብር የሚፈጸም ነው” የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ዓለምአንተ አግደው
ባሕር ዳር: መስከረም 19/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ከመስከረም 19/2017 ዓ. ም ጀምሮ ለአምስት ቀናት የሚቆይ የአማራ ክልል የዳኝነት እና የፍትሕ አካላት የትብብር እና ጥምረት የውይይት መድረክ ተጀምሯል።
በመድረኩ የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ቴዎድርስ ምህረትን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ መሪዎች ተገኝተዋል።
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ዓለምአንተ አግደው የፍትሕ አገልግሎት በአንድ ተቋም ብቻ የሚጠናቀቅ ሳይኾን በቅብብልሽ እና በትብብር የሚፈጸም መኾኑን ተናግረዋል።
የዳኝነች እና የፍትሕ አካላት ነጻነታቸውን ጠብቀው በሚያገናኟቸው ጉዳዮች ላይ በፍትሕ አሰጣጡ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች በመለየት መፍትሄ እንዲሰጡ ለማስቻል የተዘጋጀ መድረክ መኾኑን አስገንዝበዋል። ለሕዝቡ የተሻለ ፍትሕ ለመስጠትም መድረኩ አስፈላጊ መኾኑን ነው ያብራሩት።
በመድረኩ ከፌዴራሉ እና ሌሎች ተቋማትም የአሥተዳደር ፍትሕ፣ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ ጠበቆች በፍትሕ ሥርዓቱ ስላላቸው ሚና እና ስለሚያጋጥሙ ችግሮች፣ ስለወንጀል መከላከል ስትራቴጅዎች፣ በወንጀል የተገኘ ሃብትን በመለየት፣ መመርመር እና በማስመለስ፣ በሴቶች እና ሕጻናት ላይ ስለሚፈጸሙ ጥቃቶች እና ምላሽ አሰጣጥ ላይ ውይይት እንደሚደረግ ገልጸዋል።
በሥራ ላይ የቆየው በፍርድ ቤቶች ሠብሣቢነት የሚመራ የዳኝነት እና የፍትሕ አካላት ጥምረት የ2017 በጀት ዓመት የጋራ ዕቅድ በማዘጋጀት ሥራ መጀመሩን እና በዚህ ውይይትም ተጨማሪ ግብዓቶች ታክለውበት ጸድቆ ወደ ሥራ እንደሚገባ ነው ፕሬዚዳንቱ የገለጹት።
የፍትሕ ሥርዓት ማሻሻያ እና በሌሎች ስያሜዎች የፍትሕ አገልግሎቱን ለማሻሻል ሙከራዎች ቢኖሩም ኅብረተሰቡ የሚፈልገው ለውጥ አለመምጣቱን የገለጹት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንቱ ከአምስት ዓመት በፊትም የፍትሕ ተቋማቱን እንደገና ለማደራጀት ቢሞከርም ውጤቱ በሚፈለገው ደረጃ አለመኾኑን ነው የጠቀሱት።
ለዚህም በፌዴራል እና በክልል ምክር ቤቶች የሚመራ የፍትሕ ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በ2015 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እየተደረገ መኾኑን ገልጸዋል።
በውይይቱ የፌዴራል የዳኝነት እና የፍትሕ ተቋማት ተሞክሮዎች፣ አገልግሎት አሰጣጥን በቴክኖሎጅ ለመደገፍ የተሠራው ሥራ ውይይት ተደርጎበት ተሞክሮ የሚወሰድበት እና በጋራ ትብብርም የፍትሕ አገልግሎት የሚረጋገጥበት ሁኔታ እንደሚመቻች ገልጸዋል።
በውይይቱ የዳኝነት እና የፍትሕ አካላት፣ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ የክልሉ ፍትሕ ቢሮ፣ የፖሊስ ኮሚሽን፣ የአማራ ክልል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን፣ ከፍተኛ እና መካከለኛ መሪዎች፣ የዞን ፍርድ ቤቶች፣ የፍትሕ መምሪያዎች፣ የፖሊስ መምሪያዎች እና የማረሚያ ቤት ኀላፊዎች እየተሳተፉበት ነው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!





