“ሕዝብን በማሳተፍ ሕገ ወጥነትን መከላከል ይገባል” ረዳት ኮሚሽነር ውበቱ አለ

“ሕዝብን በማሳተፍ ሕገ ወጥነትን መከላከል ይገባል” ረዳት ኮሚሽነር ውበቱ አለ

ባሕር ዳር: ነሐሴ 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የምርት እና ግብይት፣ የገበያ አረጋጊ፣ ፀረ ኮንትሮባንድ እና ሕገ ወጥ ንግድ ቁጥጥር ጥምር ግብረ ኀይል የወንጀል ጉዳዮች ክትትል ቴክኒክ ኮሚቴ የ2016 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም እና የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ውይይት አድርጓል፡፡

በውይይቱ ሕገወጥነትን በቁርጠኝነት በመከላከል ሕዝብን ከችግር መታደግ እንደሚገባ ተመላክቷል፡፡

የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ የንግድ ውድድር ሸማቾች ጥበቃ እና መሠረታዊ የንግድ እቃዎች አቅርቦት ዳይሬክተር እንዲሁም የቴክኒክ ኮሚቴው አባል ታፈረ ይመር ኮሚቴው በርካታ ሥራዎችን ማከናወኑን ገልጸዋል፡፡

የሸማቾችን መብት ማስከበር እና የዋጋ ንረትን መከላከል ሥራ መሠራቱን ነው የተናገሩት፡፡ በተደረገው ሕገወጥነት የመከላከል ሥራ አሥተዳደራዊ እና ሕጋዊ ርምጃዎች የተወሰደባቸው አካላት መኖራቸውንም ገልጸዋል፡፡

የተደረገውን የኢኮኖሚ መሻሻያ እንደ አጋጣሚ በመጠቀም ሕገወጥ ተግባር የሚፈጽሙ አካላትን ለመቆጣጠር መሠራቱንም ተናግረዋል፡፡

ከኢኮኖሚ ማሻሻያው ጋር ተያይዞ ሸማቹን ማኅበረሰብ የሚጎዳ ተግባራት መፈጸም እንደማይገባም ገልጸዋል፡፡

ሕዝብን የሚጎዳ ተግባር የፈጸሙ አካላት ርምጃ እየተወሰደባቸው ነው፣ በቀጣይም ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት፡፡

ሕዝብ የሚበላው ማሳጣት በሕይወቱ መፍረድ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ ችግር የሚፈጥሩ አካላትን መቆጣጠር እና ተጠያቂ የማድረግ ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

የመከላከል ሥራው ከሕገወጥ ሥራው ቀድሞ መገኘት፣ ማኅበረሰብን ማሳተፍ ይገባል ነው ያሉት፡፡ አስተማሪ ርምጃዎች ቢኖሩም በቂ ግን አይደሉም ብለዋል ዳይሬክተሩ፡፡ ሕገወጥነትን ለመከላከል ጠንካራ እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚጠበቅም አሳስበዋል፡፡

የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር እና የኮሚቴው ምክትል ሠብሣቢ ረዳት ኮሚሽነር ውበቱ አለ ሕገወጥነትን ለመከላከል ጠንከር ያለ ሥራ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ቁርጠኝነት ያለው ጠንካራ ሥራ ካልተሠራ በስተቀር ሕዝብን መታደግ አይቻልም ነው ያሉት፡፡ ሕዝብን ከችግር ሊያወጣ የሚችል ሥራ መሥራት እንደሚጠበቅም ተናግረዋል፡፡

በኑሮ ውድነት እና በሌሎች ችግሮች የተማረረውን በቅንጅት ከምሬት ማውጣት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል፡፡

ኅብረተሰቡን በሚሠራው ሥራ ማሳተፍ እንደሚገባም ገልጸዋል። በደላላ የሚንረውን ዋጋ ሕዝብን በማሳተፍ መከላከል እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።

ከሕዝብ የሚሰጡ ጥቆማዎችን በተገቢው መንገድ መቀበል፣ በሕገወጥ መንገድ የሚሠሩ አካላት ላይ አስተማሪ ርምጃ መውሰድ፣ ለሕዝብ አስፈላጊውን ግንዛቤ መፍጠር እና ለመብቱ እንዲታገል ማድረግ ይጠበቃልም ብለዋል።

ሕገወጥነትን መከላከል የፖሊስ የተለመደ ሥራ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ በክልሉ የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር እንደ ምክንያት በመጠቀም ወደ ሕገወጥነት የሚገቡ አካላት መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡

በጸጥታ ችግር ውስጥም ኾነው በሕገወጥ ተግባር የተሳተፉ አካላትን ምርመራ አጣርተው ለሕግ ማቅረባቸውን አመላክተዋል፡፡ በሕገወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረውን ሃብት መያዛቸውንም አንስተዋል፡፡

ከኅብረተሰቡ ላይ የተጫነውን ሕገወጥ አካሄድ መቆጣጠር ይገባል ያሉት ረዳት ኮሚሽነሩ በኑሮ ውድነት ምክንያት ኅብረተሰቡ ለመኖር እየተቸገረ ነው፣ ይሄን ማስተካከል ይገባል፣ ኅብረተሰቡም የተለመደ ነው እያለ ዝም ማለት የለበትም፣ ሕገወጥ አሠራር ሲያይ ለፖሊስ ማሳወቅ ይገባዋል ነው ያሉት፡፡ የትኛውንም ሥራ ከሕዝብ ተሳትፎ ውጭ ማሳካት እንደማይቻልም አመላክተዋል፡፡

ሕዝብን እየጎዳ ያለውን ሕገወጥ አካሄድ ለመቆጣጠር ሕዝብን ተሳታፊ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡ ከሕዝብ ጋር በሠሯቸው ሥራዎች በሕገወጥ ተግባር የተሳተፉ አካላት ተጠያቂ እንዲኾኑ ማድረጋቸውንም ተናግረዋል፡፡

የገበያ ግሽበቱን የበለጠ ለማሻሻል የሸማቾች ማኅበርን ማጠናከር፣ ምርት በስፋት እንዲገባ ማድረግ ይጠበቃልም ብለዋል፡፡

ፖሊስ የሚደርሰውን መረጃ መሠረት በማድረግ ምርመራ አጣርቶ ለሕግ እንደሚያቅርብም ገልጸዋል፡፡ ፖሊስ የሚጠበቅበትን ኀላፊነት እና ግዴታ እንደሚወጣም አመላክተዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top