
በበጀት ዓመቱ ከ455 ሚሊዮ ብር በላይ በወንጀል የተመዘበረ ሃብት ማስመለሱን የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ገለጸ።
ባሕር ዳር: ነሐሴ 30/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ቢሮው በ2016 በጀት ዓመት ያከናወናቸውን ሥራዎች በተመለከተ ለአሚኮ ማብራሪያ ሰጥቷል።
የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ውጤታማ እና ተደራሽ የፍትሕ አገልግሎት በመስጠት በወንጀል ዘርፍ የሕግ የበላይነትን፣ ሰብዓዊ መብትን፣ ሰላም እና ደኅንነትን፣ በፍትሐብሔር ዘርፍ ደግሞ የመንግሥትን እና የሕዝብን ጥቅሞች ማስጠበቅ ዋነኛ ተልዕኮው ነው።
በ2016 በጀት ዓመት ከቀረቡት 16 ሺህ 910 የወንጀል መዛግብት ውስጥ 15 ሺህ 822 በአቃቢ ሕግ ውሳኔ ተሰጥቶባቸዋል።
ለዚህ ደግሞ መዝገቦችን በፍጥነት ከማጥራት አኳያ 97 ነጥብ 7 በመቶ ማከናወን መቻሉን የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኀላፊ ብርሃኑ ጎሽም አስረድተዋል።
በፍርድ ቤት ላይ ሲከራከሩባቸው ከነበሩ 17 ሺህ 732 መዝገቦች ውስጥ 8 ሺህ 633 ውሳኔ ተሰጥቶባቸዋል።
ከእነዚህ በፍርድ ቤት ውሳኔ ከተሰጠባቸው ውስጥ 7 ሺህ 637 መዝገቦች በፍትሕ ቢሮ እና በየደረጃው በሚገኙ መዋቅሮች በአሸናፊነት ያስወሰናቸው ናቸው።
ጥፋተኞችን ከማስቀጣት ባለፈ በበጀት ዓመቱ 455 ሚሊዮ 857 ሺህ 872 ብር በወንጀል የተመዘበረ ሃብት ወደ መንግሥት ካዝና እንዲመለስ ተደርጓል።
694 ሄክታር የከተማ እና የገጠር መሬትም፣ በሕገ ወጥ የተያዘ የጦር መሳሪያ፣ ነዳጅ ፣ የአፈር ማዳበሪያ፣ የምግብ ዘይት፣ አልሚ ምግብ /ፕላምፕሌት/፣ የቦንዳ አልባሳት ጭምር ለመንግሥት ገቢ መደረጉን ገልጸዋል።
የሰው ኀይል ፍሰት እና በጸጥታው ችግር ምክንያት ተከሳሽ እና ምስክር አለመቅረብ በበጀት ዓመቱ እንደ ዋና ችግር ተነስቷል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
