የአማራ ክልል የንግድና ግብይት ጥምር ግብረ ኃይል የ12 ወራት ዕቅድ አፈጻጸሙን ገመገመ።
ሐምሌ 09/2018 ዓ/ም ባህር ዳር (ፍትህ ቢሮ) የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ የምርት እና ግብይት፣ የገበያ አረጋጊ፣ የፀረ- ኮንትሮባንድ እና ሕገ-ወጥ ንግድ ቁጥጥር ጥምር ግብረ ኀይል የቴክኒክ ኮሚቴ የ12 ወራት የዕቅድ አፈፃጸም ገመገመ።
የግምገማ መድረኩን በንግግር የከፈቱት የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ምክትል ኃላፊ እና የግብረ ኃይሉ ቴክኒክ ኮሚቴ ሠብሣቢ አያሌው አባተ (ዶ/ር) የኢኮኖሚ ወንጀሎች በዋናነት የፖለቲካ አለመረጋጋት ከማምጣት ጀምሮ ውሥብሥብ የኾነ ማኅበራዊ ቀውስ ውስጥ እያስገቡ ስለኾነ በጉዳዩ ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት አስፈላጊ እንደነበረ ገልጸው።
ለዚህም የሸማቹን ማኅበረሰብ ደኅንነት ለመጠበቅ ሲባል የግብረ ኃይል አደረጃጀቱን የፌዴራል ተቋማት ባሉበት በመመሥረት ወደ ሥራ በመግባት ስራወች በየ3ወሩ እየተገመገሙ ነው የመጡት ብለዋል።
የኢኮኖሚ ወንጀሎች በዋናነት የሸማቹን ማኅበረሰብ ደኅንነት እና ጤንነት ለመጠበቅ ስለሆነ በውጤታማነት ላይ የተመሠረተ ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ብዙ ጊዜ በንግድ ዘርፍ የሚፈጸሙ ወንጀሎች የሀገሪቱን እሴት እና ባሕል የሚያጠፉ ናቸው ያሉት ምክትል ቢሮ ኃላፊው በሀገሪቱ እና በትውልዱ ላይ ትልቅ ጉዳት የሚያደርሱ መኾናቸውን ነው የተናገሩት።
ከዚህ አኳያም አደረጃጀቱ ተጠናክሮ ምላሽ ለመስጠት ሞክሯል ነው ያሉት። ሲሠሩ የቆዩ ሥራዎችም ዛሬ ተጠቃለው ይገመገማሉ ብለዋል።
በግምገማው የተገኙ ግብዓቶች ለቀጣይ በጀት ዓመት ዕቅድ በመነሻነት የሚያገለግሉ ይኾናልም ብለዋል።
በ12 ወራት የተከናወኑ ተግባራትን በዝርዝር ያቀሰቡት በአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ የኢኮኖሚ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ሙሉጌታ አሻጋሬ በግብረ ኃይል የተደራጁ 13 ተቋማት ሕገ ወጥ ድርጊቶችን በሕግ ከመጠየቅ ባለፈ በተወሰዱ አሥተዳደራዊ እርምጃዎች ከ6 ቢሊዮን ብር በላይ ለመንግሥት ገቢ እንዲኾን ተደርጓል ነው ያሉት።
በዚህ ዓመት ብቻ በአሥተዳደራዊ እርምጃ ከ263 ሺህ በላይ የንግድ ተቋማት ላይ አሥተዳደራዊ እርምጃ መወሰዱንም ገልጸዋል።
የፌዴራል እና የክልል ፖሊስ እንዲሁም የገቢዎች መርማሪዎች 1 ሺህ 612 የምርመራ መዛግብትን አጣርተው ለአቃቤ ሕግ ማቅረባቸውንም አንስተዋል። ከቀረቡት መዛግብት መካከል 1 ሺህ 410 መዛግብት ለፍርድ ቤት ቀርበው 578 መዛግብት ላይ ውሳኔ ተሰጥቷል ብለዋል። 559 የሚኾኑት በጥፋተኝነት ሲወሰኑ 19 የሚኾኑት ደግሞ ነጻ ተብለዋል ነው ያሉት።
ጥፋተኞቹ እስከ 12 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ተደርጓል፤ ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብ መቀጮ ተጥሏል፤ ከ798 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ ንብረት በኤግዚቢትነት ለመንግሥት ገቢ ኾኗል ብለዋል። በሰው ጤና ላይ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ ከ197 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ ምግብ እና መድኃኒቶች በፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንዲወገዱ ተደርጓልም ነው ያሉት።
በአሥተዳደራዊ እርምጃ፣ በመቀጮ እና በኤግዚቢት በድምሩ ከ7 ቢሊዮን ብር በላይ ለመንግሥት ገቢ መኾኑንም ገልጸዋል። ይህም የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት እና ከሕጋዊ አሠራር የሚመነጭ የግብር ገቢን ከፍ ለማድረግ ትልቅ ሚና አለው ነው ያሉት።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የልዩ ልዩ ወንጀል ምርመራ ዋና መምሪያ ኀላፊ ኮማንደር ደጀን ወዳጅ ለክልሉ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ከቀረቡ 1 ሺህ 76 ልዩ ልዩ የክስ መዝገቦች መካከል 85 በመቶ የሚኾኑት በሕግ እንዲጠየቁ ተደርጓል ብለዋል።
ከእነዚህ ውስጥ 163 የሚኾኑት ክሶች በአሁኑ ወቅት በፖሊስ እጅ ይገኛሉ ነው ያሉት።
ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት ደግሞ 236 የተሰወሩ ተከሳሾች እንዳሉ እና በቀጣይ እነዚህን ተከሳሾች በማደን ለሕግ ለማቅረብ ፖሊስ በትኩረት እንደሚሠራም ገልጸዋል።
በዚህ በጀት ዓመት ብቻ ፖሊስ ከ366 ሚሊዮን ብር በላይ ሊባክን የነበረ የመንግሥት እና የሕዝብ ገንዘብ ማዳን ችሏልም ብለዋል።
የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ምክትል ኀላፊ እና የግብረ ኃይሉ ቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ አያሌው አባተ (ዶ.ር) በግብረ ኃይሉ የተደራጁት 13ቱ ተቋማት የጸጥታ ሁኔታው ሳይበግራቸው በአንድ ልብ መሥራታቸውን ተናግረዋል። የተሠራው የኢኮኖሚ ወንጀሎችን የመከላከል ሥራ የክልሉን የ25 ዓመት የእድገት እና ዘላቂ ልማት አሻጋሪ ዕቅድ መሠረት ያደረገ መኾኑንም ጠቅሰዋል።
በቀጣይ በጀት ዓመትም የፍትሕ ሥርዓቱን ይበልጥ ለማጠናከር መሥራትን ጨምሮ በልዩ ሁኔታ በማዕድን ሀብት፣ በሕገ ወጥ የእንስሳት ግብይት እና በሕገ ወጥ ንግድ ላይ ያተኮረ ሥራ እንደሚሰራም አመላክተዋል።







Great and thank you for such fresh news
ok thanks too