የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ የ2017 ዓ.ም ዘመን መለወጫ በዓልን ምክንያት በማድረግ ለታራሚዎች ይቅርታ መደረጉን አስታወቀ፡፡

የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ የ2017 ዓ.ም ዘመን መለወጫ በዓልን ምክንያት በማድረግ ለታራሚዎች ይቅርታ መደረጉን አስታወቀ፡፡

የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ምክትል ቢሮ ኀላፊ ወንዳቸው ሠራው የ2017 የዘመን መለወጫን ምክንያት በማድረግ ለታራሚዎች ይቅርታ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ከተሰጡት ሥልጣን እና ተግባራት ውስጥ በይቅርታ ሊፈቱ የሚገባቸውን ዜጎች በቦርድ ዓይቶ ለአሥተዳደር ምክር ቤቱ አቅርቦ ማስወሰን ነው ብለዋል።

በዚህም ምክንያት የክልሉ መሥተዳድር ምክር ቤት ጳጉሜን 3 ቀን 2016 ዓ.ም ባደረገው 6ኛ ዙር 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ሥብሠባ በ2017 ዓ.ም የ1ኛ ዙር ይቅርታን ምክንያት በማድረግ የክልሉን የይቅርታ መሥፈርት አዋጅ 136/1998 እና ይህንኑ ለማስፈጸም በወጣው መመሪያ ቁጥር 33/2010 መሠረት 1 ሺህ 389 ወንድ እና 41 ሴት በድምሩ ለ1 ሺህ 430 ታራሚዎች ይቅርታ ተደርጓል ብለዋል።

ይህም በክልሉ ማረሚያ ቤቶች ለሚገኙ ታራሚዎች ከመሥከረም 1/2017 ዓ.ም ጀምሮ እንዲለቀቁ መወሰኑን ገልጸዋል።

የይቅርታው መስፈርቶች

👉 ከአሁን በፊት ወንጀል ፈጽመው በክልሉ ፍርድ ቤቶች የተቀጡ፣

👉 በግልጽ በሕግ ይቅርታን በተመለከተ ያልተከለከሉ፣

👉 በማረሚያ ቤት ቆይታቸው የታረሙ እና በባህሪያቸው የተለወጡ፣

👉 በፍርድ ቤት ከተቀጡ በኋላ በመመሪያው መሠረት ዝቅተኛውን የእሥራት ጊዜ የተቀጡ፣

👉 የይቅርታ አወሳሰን መመሪያው እርቅ ያስፈልጋቸዋል ብሎ ባመነባቸውን ጉዳዮች እርቅ የተፈጸመ እና ለተበዳዮቹም ካሣ የተከፈለ መኾኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት፣

👉 ዜጎቹም ለወደፊት አምራች እና ሕግ አክባሪ ኾነው ማኅበረሰቡን ይጠቅማሉ ተብሎ የታመነባቸው መኾኑን አቶ ወንዳቸው ዘርዝረዋል።

ከእሥር የሚለቀቁ በቀጣይ ደግሞ ይቅርታ ያገኙ ተብለው የሚጠሩት ታራሚዎችም የሚጠበቅባቸው፦

👉 የፈጸሙት ወንጀል ሕዝብ እና ሀገርን የሚበድል ስለኾነ ሕዝብ እና ሀገርን መካስ እንደሚጠበቅባቸው፣

👉 ከማረሚያ ቤት ሲወጡ ታርመዋል፤ አምራች ኾነዋል፤ የሕግ የበላይነትን አውቀዋል ተብሎ ስለሚታመን ከመሰል ወንጀሎች ራሳቸውን መጠበቅ፣

ሌላው የኅብረተሰብ ክፍል ከእነርሱ ተምሮ ወንጀሎችን እንዳይፈጽም አስተማሪ እና አርዓያ መኾን ነውም ብለዋል።

እነዚህንን መሠረት በማድረግም የክልሉ መንግሥት ከመሥከረም 1/2017 ዓ.ም ጀምሮ ይቅርታ ያደረገ መኾኑን ምክትል ቢሮ ኀላፊው አስታውቀዋል።

አሚኮ

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top